አዲስ አበባ – ራዕይ የህጻናት መርጃ ድርጅት ለአእምሮ እድገት ውስንነት ላለባቸው ህፃናት ከውጭ ሀገር ያስገባቸው ኮምፒውተሮች፣ የሙዚቃ መሳሪያዎች እና ሌሎች አጋዥ እቃዎች ከአምስት ዓመታት በኋላ ከኤርፖርት ጉምሩክ መለቀቃቸው ተገለጸ።
እነዚህ እቃዎች ለልዩ ፍላጎት ያላቸው ህፃናት የተዘጋጁ ቢሆኑም፣ በወቅቱ የነበረው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ከመንግስታዊ ተቋማት የሚያስፈልጉ ፈቃዶችና የድጋፍ ደብዳቤዎች ማምጣት በመዘግየቱ ለአምስት ዓመታት በጉምሩክ መጋዘን ውስጥ ተቀምጠው ቆይተዋል።
ነገር ግን፣ የአዲስ አበባ ኤርፖርት ጉምሩክ እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኃላፊዎች እቃዎቹ ቀጥታ ለህፃናት እንደሚደርሱ በመገንዘብ እና ሁኔታውን በማስተዋል እንዲለቀቁ ውሳኔ አስወስነዋል። በዚህም መሠረት እቃዎቹ ጥቅምት 4 ቀን 2018 ዓ.ም ለድርጅቱ ተረክበዋል።
የድርጅቱ መስራችና ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር ጽጌ ጥበቡ ለእቃዎቹ መለቀቅ አስተዋጽኦ ያደረጉ የጉምሩክ ሰራተኞች፣ ተቋማት እና ግለሰቦች ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የተለቀቁት እቃዎች በአዲስ አበባ ውስጥ ከ300 በላይ ለሚሆኑ የአእምሮ እድገት ውስንነት ያላቸው ተማሪዎች ለማገልገል ይውላሉ። እነዚህም ተማሪዎች በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ የማነ ብርሃን፣ ትንቢተ ኤርሚያስ እና ወይራ የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤቶች እንዲሁም በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ስብስቴ ነጋሲ ት/ቤት ይገኛሉ።
ድርጅቱ በተጨማሪ በአዳማ ከተማ የሚገኘው ሌተናል ኮሎኔል ደጀኔ ስሜ የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት ግቢ ውስጥ ለልዩ ፍላጎት ያላቸው ህፃናት የእንክብካቤ ማዕከል ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ መጣሉን አስታውቋል።
ራዕይ የህጻናት መርጃ ድርጅት በ2007 ዓ.ም በዶ/ር ጽጌ ጥበቡ የተመሰረተ ሲሆን፣ ለአእምሮ እድገት ውስንነት እና ሌሎች የአካል ጉዳት ያላቸው ህፃናትና ወጣቶች በትምህርት፣ በሙያ፣ በመንፈሳዊና በስሜታዊ ድጋፍ ማድረግን ዓላማው አድርጎ ይሰራል።
በመጨረሻ፣ የድርጅቱ የበጎ ፈቃድ አምባሳደር አትሌት መሠረት ደፋር ለህፃናት የምታደርገው ድጋፍ ልዩ አድናቆትና ምስጋና ይገባታል ተብሏል።
Spread the Word
Help us amplify our message by sharing this story with your network.
